Popular Posts

Friday, October 14, 2011

ትልቁ እንጀራ*

እንጀራ ሊጋግሩ
ሰዎች ተሰበሰቡ
ኩበት ፋንድያ ለቀሙ
ግፋፉ እንጨት ሰበሰቡ::
..................................
ዱቄቱ ተፈጭቶ ተቦክቶ
ትልቅ እንጀራ ተጋገረ
ታዲያ ይኼኔ ሰው ሁሉ
"ሻሞሽ ሻሞሹን ጀመረ::
ህብረቱ ተበታተነ
ስብሳቦሹ ፈራረሰ
የሁሉም እጅ ያነኮረው
እንጀራው ተፎረፎተ
እንጀራው ተቆራረሰ::
//---//
*"ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ" የሚባለው ትዝ አላችሁ?
ጥቅምት 2 2004 ዓ.ም
የ አ.አ.ዩ መምህራን ጠቅላላ "ስብሳቦሽ" ላይ ሆኜ
(ይህችን ግጥም በመጻፍ ስብሳቦሹን የማስታጉል እንጀራውን የማነኩር አንድ እኔ ነኝ??)

አትልፊ ሆዴ!!

አይኖቼን ብትወጊያቸው
በልቤ አይኖች አይሻለሁ
ልቤን አቁስለሽ ብታደሚው
በምናቤ እቀርፅሻለሁ::
ከውስጡ ልጥፋ ብለሽ
በከንቱ አትፍጨርጨሪ
ራስሽን እንኳ ብታጠፊ
ውስጤ ነው ምትቀበሪ*::
//--///
*መቀበር በዚህ አግባብ መሞትን ወይም መቛጨትን እንዲያሳይ አልፈልግም:: ይልቅስ ማረፍ (መጠለል) እና ደግሞ መሰንቀር ወይም መቀርቀር(ለምሳሌ የወሊድ መቆጣጠሪያ ወይም የ...........መድሃኒት እንደሚቀበር) በሚሉት ትርጓሜዎች ይታሰብልኝ::
ሆዴ የተባልሽ ሁላ.......ግን እውነት ይመስልሻል?
ጥቅምት 2 2004 ዓ.ም
ከሰዓት
FBE አድራሽ
ስብሰባ ላይ ሆኜ(ስብሰባውን አቋርጨ በሀሳብ መንጎዴ የተገባ ነው?)

Saturday, August 6, 2011

እግዜር ይስጥልኝ ሰይጣን!!


ሰይጣን እወደሃለሁ ብዬ ባልደልልህም
ላስተማርከኝ ነገር ሁሉ ሳላመሰግን አላልፍም::
አንተ ባትፈታተነኝ በድካሜ ባልኮንታኮት በውድቀቴ ባልሰበር
አንዳንተው ትዕቢቴ ጥሎኝ ከክፉው ሲኦል ተጥዬ እነድ እሰቃይ ነበር::
ሐሙስ ሐምሌ 29 2003 ዓ.ም

የተሸወድኩት

ሸወድሽኝ ተጫወትሽብኝ
ቀለድሽብኝ አጃጃልሽኝ አቂቂያልሽኝ
እንዲህ እንዲያ ዚኒ ቁልቋል
ገለ መለ አልልሽም
ምክንያቱም አንቺ አይደለሽም::
እኔ ነኝ የተሸወድኩት
ለ እግዚአብሄር መሰውያው ላይ
ራሴን ላንቺ ያረድኩት
ላምላኬ በማጠኛው
ራሴን ላንቺ ያጠንኩት::
እኔ ነኝ የተሸወድኩት
በዚች የ እግዚአብሄር ልቤ ውስጥ
"አንቺ"ን ከ "እርሱ" ያዳበልኩት::
እኔ ነኝ የተሸወድኩት
በ እግዚአብሄር ቅዱስ ስፍራ ላይ
የክብር ጫማዬን አውልቄ
ላንቺ ክብር የሰገድኩት::
እኔ ነኝ የተሸወድኩት
ለሞተልኝ አምላኬ ሳይሆን
ለሞትኩልሽ ላንቺ የሞትኩት::

እንዲህ እንዲያ ዚኒ ቁልቋል አልልሽም
ምክንያቱም አንቺ አይደለሽም::
እኔ ነኝ የተሸወድኩት
ትልቁን "ፈጣሪዬን" ትቼ
ትንሿን "ፍጡር" ያመለኩት::

//--///
ሐምሌ 27 2003
ሳር ቤት እቤት
ሴቶችን "ለሚያመልኩ" "ላመለኩም" ሁሉ::

Wednesday, July 27, 2011

ማን እንደኔ

ማን እንደኔ ይሆናል?
ማንስ እኔን ይመስላል?
ከ አላዛር እበልጣለሁ
ከ ኢየሱስም እልቃለሁ
በየጊዜው እየሞትኩኝ
በየጊዜው እነሳለሁ::
//-//
(To "the old self, the old man" which dies and rises now and then!

To us who fall and rise every time)__sorry for the GURAMAYLE!
ሐምሌ 18 2003 ዓ.ም
4:45 ከ ምሽቱ
አፍንጮ በር
ሃሳቡ ቀደም ብሎ ቀን ላይ ተፀንሶ ነበር

Monday, July 25, 2011

ኦ ማንዴላ

ኦ ማንዴላ
የማትሰክር በጠላ
በአረቄ የማትጠነብዝ
በወይን የማትደነዝዝ::
ያን ሁሉ ስቃይ ተግተህ
ያን ሁሉ ግፍ ጠጥተህ
ሰክረህ ያልተንገዳገድከው
ይኸ ድንቅ አምላካችን
ምን ማርከሻ ቢሰጥህ ነው??

ኦ ማንዴላ
የማትሰክር በጠላ
በአረቄ የማትጠነብዝ
በወይን የማትደነዝዝ
ያን ሁሉ ዝና ጨልጠህ
ያን ሁሉ ክብር አንዶቅዱቀህ
በስልጣን አረቄዋ
በናላ አዟሪዋ እጅ ወድቀህ
ሰካራም ሆነህ ያልቀረኸው
ይኸ ግሩም ጌታችን
ምን ማርከሻ ቢሰጥህ ነው??
//-///
ሐምሌ 17 2003 &ወደ ምሽት( ነገ የ ማንዴላ 93ኛ ዓመት የልደት በዓል ይከበራል)
ፒያሳ& ኪያብ ካፌ
ከወዳጄ በረከት ጋር ስለ ማንዴላ አውርተን ውስጤ ቢነሳሳ ጊዜ ጻፍኩት
ለማንዴሎች ሁሉ ጌታ ለጌታ ኢየሱስ!!

Saturday, July 23, 2011

ነገረ-ቆብ

እውቀትን መረመርናት

ውስጠ ሚስጥሯን በልትናት

እንኳን ደስ ያለን ያሉ

የራስ ቆብ ይደፋሉ::

ደግሞ

አለምን ብንመርምር

ደስታን ከሀዘን ብንደምር

"ችቦ አይሞላም ወገቧ"

ከንቱነት ነው ቀለቧ

ትቅርብን እንፍታት ያሉ

የራስ ቆብ ይደፋሉ::

//---///

ሓምሌ 16 2003 ዓ.ም

7:58 ከሰዓት

እንቁላል ፋብሪካ

ለወዳጄ ለ ኢየሩሳሌም አሰግድ ምርቃት ግብጃ ሄጄ የጫርኩት

Saturday, July 16, 2011

ዱቤ 1

እግዚአብሄር ዱቤ ይወዳል
ፀሎት በዱቤ ይወስዳል
ግን አይደለም እንደ ሰው
በጊዜው በሰአቱ
ጨምሮ ነው ሚመልሰው::

ሓምሌ 5 2003 ከሰዓት
አፍንጮ በር አዲስ አበባ
በስራ ተወጥሬ መጣብኝ

Saturday, July 9, 2011

ሀገሬ በሰማይ?

"ሀገሬ በሰማይ ነው" ብዬ ፎክሬ ዝቼ
"ሀገሬን ከነጣጣዋ" "ለምድራውያኑ" ትቼ
ወደ ሰማያ ተነጥቄ ደጆቿን ብነካካ
"ወደ ምድር ሂድ" ተባልኩ
የአንድዬ አላማ
"ግዛት ማስፋት" ነው ለካ!

ሀምሌ 1 2003 ዓ.ም
6 ኪሎ ድህረ ምረቃ በተ-መጻህፍት